የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው — ጥናት

የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናት አመለከተ

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከ17 ሺህ በላይ ባለሃብቶች በዘርፉ ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ ቢሆንም ወደ ተግባር የተሸጋገሩት አንድ ሺህ 837 ናቸው ተብሏል።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሞተርነት ሚናውን ከመጫወት አኳያ ያሉት ዕድሎች፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያካሄደውን ጥናት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በ1994 ዓ.ም በወጣው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ ላይ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት ሞተር እንዲሆንና መንግስትም የባለሃብቱን አቅም መገንባት እንዳለበት ተቀምጧል።

በዚህ መሰረት በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በዘርፉ እያደረገ ያለው ተሳትፎ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ጥናት ማድረግ አስፈልጓል ነው የተባለው።

በማዕከሉ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አማረ ማተቡ "በአምራች ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ሲባል ዘርፉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት ከፍተኛ እሴት በመጨመርና ሃብት በመፍጠር ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ጉልህ ሚና ስለሚጫወት ነው" ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የተለየ ማበረታቻና ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በዘርፉ አንቀሳቃሽ ሞተርነት ሚናውን እየተጫወተ አለመሆኑ በጥናቱ መረጋገጡንም ነው ዶክተር አማረ ያስረዱት።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን በምሳሌነት በማንሳት።

እንደ ዶክተር አማረ ገለጻ በዘርፉ ለመሰማራት ፈቃድ የወሰዱ አንዳንድ ባለሃብቶች አጥር ብቻ አጥረው ቆመዋል፤ ሌሎቹ መጋዘን ገንብተው ለዕቃ ማከማቻነት ተጠቅመውበታል።

አንዳንዶቹ ምንም እንቅስቃሴ የላቸውም፣ የተወሰኑት ደግሞ የተሰጣቸውን መሬት ለሌላ ተግባር ማዋላቸውንና ጥናቱ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከሚገጥማቸው ችግሮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹን መለየቱንም ተናግረዋል።

የአሰራርና የአፈጻጸም ክፍተት፣ የአመራሮችና ባለሙያዎች የአፈጻጸም አቅም ትኩረት ማነስ፣ የአሰራር ስርዓት አለመኖርና ተቀናጅቶ አለመስራት የችግሮቹ መሰረታዊ መንስኤዎች መሆናቸውን ዶክተር አማረ አብራርተዋል።

በጥናቱ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ተነስተዋል።

ዘርፍ የለየ የወለድና የገቢ ግብር ምጣኔ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ፣ የገቢ ምርት ለሚተኩ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት ቀረጥ ታክስ ፖሊሲን ማሻሻል፣ የባለሃብቱን ምርታማነትና አቅም ለማሳደግ የሚረዳ የምርታማነት ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ማዘጋጀትና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል የሚሉት ይገኙበታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተመራው የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጥናቱ ውጤቶች ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።

በጥናቱ በአግባቡ አልተዳሰሱም የተባሉ ጉዳዮችም በተሳታፊዎቹ ተነስተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ እንዳሉት በትራንስፎርሜሽኑ የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ ተሳትፎ አናሳ የሆነበት ምክንያት እንደ ትልቅ ስትራቴጂ አለመታየቱ ነው፡፡

ስትራቴጂውን ለማሳካት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት አለመኖሩም ለተሳትፎው ማነስ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነም ያምናሉ፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውም የሀገር ውስጥ አምራች ባለሀባቱ ምርቶቹን ለምን እንደማይገዛው የሚያነሳው ጥያቄ መመለስ ቢኖርበትም አምራቹም ከሀገር ውስጥ እንዲገዛ የሚያስገድደው ህግ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍፁም አረጋ ደግሞ በማምረቻው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ተሳትፎ ማጎልበት የሚቻለው  የባለሀብቱን እውቀት ማጎልበት ሲቻል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሃዬ በበኩላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በዘርፉ ያለው ተሳትፎ የሚያድገው በአለምአቀፍ ደረጃ ያለውን ተወዳዳሪነት ሲጨምር ነው ብለዋል። መንግስት ባለሃብቱን በበቂ ደረጃ ሊደግፈው እንደሚገባ በመጠቆም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥናቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በዘርፉ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ የሚያግዝ ነው ብለዋል። 

በጥናቱ ውጤቶች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከተወያዩበትና የጋራ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ የፖሊሲ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የገለፁት።

ለጥናቱ አስፈላጊው መረጃ የተሰበሰበው ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሲሆን 255 ተቋማትና ከ457 በላይ ግለሰቦች ተሳትፈዋል- (ኢዜአ) ።