ለኢንተርፕራይዝ አምራቾች የተሰጡ ከ6 ሺህ በላይ ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ተላልፈዋል

ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መስሪያ ተብለው ለተጠቃሚዎች የተሰጡ 6 ሺህ 85 ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ለሶስተኛ ወገን ተላልፈው የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ ።

የኤጀንሲው የስራ ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስቱ፤ሆኖም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለህገወጥ ተግባር የዋሉ ከ6ሺ በላይ ሼዶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከነዚሁም ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ካርታ ወጥቶባቸው መኖሪያ ቤት የሆኑ እና ላልተፈለጉ ተግባራት የዋሉም እንዳሉ አመልክተዋል  ።

የመስሪያ እና የመሸጫ ሼዶችን ለህገወጥ ተግባር የሚያውሉና ለዘመዶቻቻው ያለአግባብ የሚሰጡ አመራሮች መኖራቸው መረጋገጡን ነው የጠቆሙት ።

ከፈዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ በ2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጀንሲ ለሥራ ፈጠራ በሚል ለተጠቃሚዎች ያስተላለፋቸው 627 ሼዶች በህገወጥ መንገድ ለሶስተኛ ወገን መከራየታቸውን ያሳያል።

በዚህ ተግባር በተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደም ነው ያሉት  ።

የኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬከተር አቶ አወሉ አብዱ፤ መንግስት ለስራ ፈጠራ ብሎ ለተጠቃሚዎች ከሰጣቸው የመስሪያ እና የመሸጫ ሼዶች 5 ሺህ 824 የሚሆኑት ለህገ ወጥ ተግባር መዋላቸው ገልጸዋል ።

ከእነዚህ ውስጥ 824ቱ የመኖሪያ ቤት ካርታ ወጥቶባቸው እንዲሁም ለሶስተኛ ወገን ተላልፈው የተገኙ ሲሆን የተያዙትም በዚሁ በመጋቢት ወር መሆኑን አስታውቀዋል ።

ክልሉ ባደረገው ክትትል 429ኙ ተነጥቀው ለሌሎች ተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ሌሎች 5 ሺህ ሼዶች በህገ ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸው በመረጋገጡ የመንጠቅ ስራ መጁመሩን አስታውቀዋል ።

በአማራ ከልል ደግሞ በአቸፈር ወረዳ 104 የማሳያ ሱቆች ለሶስተኛ ወገን ተላልፈው መያዛቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጀ አቶ በላይ ዘለቀ ናቸው።

በባህርዳርም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ለስራ ፈጠራ በሚል ከክልሉ መንግስት የወሰዱትን 300 ካሬ ሜትር ይዞታ ለሌላ ግለሰብ ሸጠው በተገኙት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የመስሪያ ቦታዎች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጊዲና ሃይለስላሴ ፤ አሁን ላይ በህገ ወጥ መንገድ የተላለፉት ሼዶች እየተመለሱ ነው ብለዋል።

በህገ ወጥ መልኩ ተላልፈው የተገኙ የመስሪያ ቦታዎችን ከማስመለስ ጎን ለጎን በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አመራሮችን ተጠያቂ ለማድረግ ቡድን ተቋቁሞ ማጣራት መጀመሩን ነው ያስታወቁት ፡፡

በመላ ሀገሪቱ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ 1 ሺህ 410 ህንጻዎች እና 24 ሺህ 93 ሼዶች ተገንብተው እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዘርፎች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት ተደራጅተው ለሚሰሩ ተጠቃሚዎች መተላለፋቸው ለማወቅ ተችሏል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።