ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውለው ሁለተኛው ዙር ቶምቦላ ሎተሪ በገበያ ላይ ዋለ።
የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ፤ ቶምቦላ ሎተሪው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ገበያ ላይ ይውላል።
ከቶምቦላ ሎተሪው እስከ 100 ሚሊየን ብር ለማሰብሰብ ታቅዷል።
እስካሁን 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የመኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪዎች፣ ፍሪጅና መሰል ለእድለኞች የሚሰጡ ሽልማቶች ተገኝተዋል።
ሽልማቶቹን የግል ባለሀብቶችና የተለያዩ ተቋማት ያበረከቱት ሲሆን አጠቃላይ ግምታቸውም እስከ 20 ሚሊየን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል።
የቶምቦላ ሎቶሪው ባለ ሦስት መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርታማ መኖሪያ ቤት፣ የ2016 ስሪት ሃይሉክስ ባለሁለት ጋቢና ተሽከርካሪ፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ዘመናዊ አፓርታማ መኖሪያ ቤት እንዲሁም አንድ ሊዮንቺኖ የማቀዘቀዣ የጭነት መኪና ሽልማቶችን ያስገኛል።
ከእነዚህም በተጨማሪ የእርሻ ትራክተር፣ ባለሶስት እግር ባጃጆች፣ ማቀዘቀዣዎች፣ የውሃ ማጣሪያዎች፣ ላፕቶፖች፣ 32 ኢንች ኤል ኢዲ ቴሌቪዥኖች እና ስማርት ስልኮች ለባለ እድለኞች ይበረከታሉ።
ከመጀመሪያው የህዳሴው ግድብ ሎተሪ ሽያጭ በሀገሪቱ በሎተሪ ሽያጭ ከፍተኛ የሆነ 64 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።