የትግራይ ሰማዕታት ሐውልትን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ በ700 ሚሊየን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማከናወን መታቀዱ ተጠቆመ።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሜነህ ግርማይ እንደገለጹት፤ የልማት ሥራዎቹ በሀውልቱ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
ለልማት ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላትና ደጋፊዎች መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጀትና ዕቅዱን የማስገምገም ሥራ መከናወኑን የገለጹት አቶ ወንድሜነህ፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት በሰማዕታት ኃውልቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዘመናዊ ሕንጻዎች ቅርጻቸውና ይዘታቸው ሳይቀየር ጥገና እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።
የጥገና ሥራው በከፍተኛ የኃውልትና ቅርስ ጥገና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን፤ በሐውልቱ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በመሰብሰቢያ አደራሾችና ቅርሶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ጥገናው እንደሚከናወንም ነው ስራ አስኪያጁ ያመለከቱት።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በሐውልቱ ግቢ ውስጥ መሰራት የነበረባቸውና ሳይሰሩ የቀሩ ተጨማሪ የግንባታ ሥራዎች እንደሚካናወኑ አስታውቀዋል።
"አዲስ ከሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎች መካከል የህጻናት መዝናኛ፣ መዋኛና የልዩ ልዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራዎች ይገኙበታል" ብለዋል።
የህወሓትና የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ታሪክ የሚጠበቅበት ማዕከል እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ የክልሉ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የሚሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ለዚህም በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት።
በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የትግራይ ሰማዕታት ኃውልት በ108 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፥ በየዓመቱ በአማካይ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኝ ስራ አስኪያጁ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።