ባለፉት ስምንት ወራት ከ936 ሺ በላይ ለሚሆኑ የአገሪቱ ወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠሩን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
ሚኒስቴሩ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት እንደገለጸው በአገሪቱ በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በሥራ አጥነት መመዝገቡን ተናግሯል ።
ዘንድሮ በሚኒስቴሩ የተፈጠረው የሥራ ቁጥር ከሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር አንጻር ሲታይ በጣም ዘቅተኛ መሆኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል ።
ሚኒስቴሩ በበኩሉ በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ውስጥ የተጠናከረ ሥራ እንደሚያከናውን ለምክር ቤቱ ገልጿል ።
ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ መንግሥት የመደበውን የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ በቀሪዎቹ ወራት ክልሎች ባላቸው ሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር የመጀመሪያ ዙር ብድር ሥርጭት እንዲውል ተደርጓል ብሏል ሚኒስቴሩ ።
ለተንቀሳቃሽ ፈንዱ ጥቅም ላይ ለማዋል በተዘረጋው የብድር አስተዳደር ማዕቀፍና መመሪያ ላይ ሥራውን ለሚመሩ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች፣ ለክልልና የከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት አመራሮች እንዲሁም ለሥራ ፈጠራ ተቋማት ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተካሄደዋል ።