በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ድርጅት በአገር ውስጥ የሚደረጉ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያጠናክር ተገለጸ ።
የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ድርጅት በአገር ውስጥ የንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ለሚደርሱ ስጋቶች የመድህን ዋስትና በመሥጠትም የጎላ ሚና እንደሚጫወት ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል ።
አፍሪካ የንግድና ኢንቨስተመንት መዳረሻ እንዳትሆን ከሚፈታተኗት ማነቆዎች መካከል የሰላምና ፀጥታ ችግር፣የፖለቲካ ቀውስ፣ የብድር አቅርቦት ማነስና ሌሎች ተጠቃሾች ችግሮች እንዳሉ ይገልጻል ፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ የአፍሪካ ሀገራት እኤአ በ2001 የአፍሪካ የንግድ ኢንሹራንስ ድርጅት ድርጅትን በዓለም ባንክ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ አማካኝነት በማቋቋም የተለያዩ የተግባር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
ድርጅቱ ባለሀብቶች በአፍሪካ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለንብረት ከለላ በመስጠት ፣በንብረት ላይ ለሚደርስ አደጋ ዋስትና እየሠጠ ይገኛል ፡፡
በአፍሪካ ሃገራት ለሚከናወኑ የንግድ እቅስቃሴዎች የፋይናንስ እጥረትን እየደጎመ መሆኑ ተገልጿል ፡፡
ኢትዮጵያም ከአራት ወራት በፊት የድርጅቱ አባል ሀገር በመሆን ከወዲሁ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞቹን ለማግኘት እየተዘጋጀት መሆኑ ተመልክቷል ፡፡
በኢንሹራንስ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ ለዋሚኮ እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድ ኢንሹራንስ ድርጅት አባል መሆኗ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል።
የመድህን ዋስትና ባለሙያ የሆኑት አቶ አሰግድ ገብረ መድህን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል በመሆኗ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሠማሩ አካላት ብድር በመሥጠትና ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላ በመሥጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።
የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ድርጅት እኤአ በ2003 ሥራ የጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 አገራት አባላት ያሉትና እስካሁንም 25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለአባል አገራቱ ወጪ ማድረግ ችሏል ።
( አርታኢ -ሰሎሞን ተስፋዬ )