አየር መንገዱ በዘመናዊው ኤር ባስ አውሮፕላን ወደ አቡጃ ሊበር ነው

ኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው ኤር ባስ ኤ350-900 ዘመናዊ አውሮፕላን ወደ ናይጄሪያ አቡጃ በረራ ሊያደርግ ነው።

በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቡጃው አውሮፕላን ማረፊያ በድጋሚ መከፈትን ተከትሎ ነው በዘመናዊ አውሮፕላን ወደ ስፍራው በረራ የሚያደርገው።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም "አየር መንገዱ የፓን አፍሪካ አየር መንገድ ከመሆኑ ባሻገር መላው አፍሪካንና የተቀረውን ዓለም በመገናኘት ለአህጉሪቱ ሁልጊዜ የኩራት ምንጭ ነው" ብለዋል።

አየር መንገዱ ወደ ናይጄሪያ በረራ የጀመረው በ1960ዎቹ አገሪቱ ከቀኝ ግዛት ተላቃ ነፃ አገር መሆኗን ተከትሎ ነው።

በናይጄሪያ ለመጣው ታሪካዊ እድገት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረው አገሪቱ በምታስመዘገበው ዕድገት አየር መንገዱ ሁነኛ አጋር ነው ብለዋል።

በአየር መንገዱ የ70 ዓመት ታሪክ የኩራት ምልክት ነው የተባለለት ኤር ባስ A350-900 ለተሳፋሪዎች ልዩ ልዩ የደረጃና የቅንጦት አገልግሎቶችን በመስጠት በረራውን ወደ አቡጃ እንደሚያደርግና የአፍሪካ አገራትን ማስተሳሰሩን እንደሚቀጥል አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ አራት ከተሞች ሌጎስ፣ አቡጃ፣ ኡኑጉ እና ካኑ በሳምንት ወደ 20 በረራዎች ያደርጋል።

ዘመናዊው ኤር ባስ A350 አውሮፕላን በአፍሪካ ሰማይ ላይ በረራ ሲያደርግ የመጀመሪያው ሲሆን አየር መንገዱ ካዘዛቸው 14 ዘመናዊ የኤርባስ አውሮፕላኖች መካከል ሶስቱ በስራ ላይ ይገኛሉ።( ኢዜአ)