በአገሪቱ በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የምርታማነት እንዲሁም የግብርና ምርት ግብይት ላይ የሚታየውን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ የሚያስችሉ 100 ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር እያሱ አብርሃ ለዋሚኮ እንደገለጹት የግብርና ግብዓቶችን ፣ የፀረ ተባይ መድሓኒቶችን ወደ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለማጓጓዝ የሚያግዙ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል ።
ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአገሪቱን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን እንዲደግፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል ሚኒስትሩ ።
አርሶ አደሩን ከዝቅተኛ የግብርና አምራችነት ለማላቀቅ ለግብርና ምርታማነትና ለግብርና ውጤቶች ግብይት ወሳኝ የሆኑ ቁሳቁሶችና ግብዓቶች ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባባር ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚደረግ መሆኑን ሚንስትሩ አስረድተዋል ።
የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ የተጣለውን ግብ እንዲመታና ዕቅዱን ለማሳካት በግብርና ዘርፍ ብቻ 8 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅበት ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል ፡፡
በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዓመት ላይ የግብርናው ምርት በእጥፍ እንዲጨምር ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ መናገራቸውን ዋልታ ሚዲያ ኮርፖሬት ዘግቧል ።