በጎንደር ከተማ በሁለት ቢሊዮን ብር የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በጎንደር ከተማ በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው የጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው ለፋብሪካው የመሰረት ድንጋይ መጣሉ የክልሉ መንግስት የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄ ለመፍታት ቁርጠኝነቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በተዘጋጀው ሥነስርአት ላይ እንደገለጹት፣  በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት የነበረውን ዝቅተኛ የኢንዱስትሪ ልማት አፈጻጸም ለመቀየር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

አፈጻጸሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስም የባለሃብቶችን ተሳትፎ ከማጠናከር ባለፈ አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክስዮን ማህበር ተቋቁሞ ወደሥራ እንዲገባ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ሰሜን ጎንደር ሰፊ የልማት መሬት፣ ውሃና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣  በተለይ ለፋብሪካው ግብአትነት የሚውለውን ጥጥ አርሶአደሩና ባለሃብቱ አምርቶ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የፋብሪካው የኢንቨስትመንት ወጪ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው በ56 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

የጎንደር  ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል አምራች ኢንዱስትሪዎች በከተማው በብዛት እንዲኖሩ የሚያስችል ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በአካባቢው አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አድርገዋል፡፡(ኢዜአ)