በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና መራቆትን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ ከጥር 1/2009 ዓ.ም ጀምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን አስታወቋል ፡፡
በሚኒስቴሩ ከፍተኛ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ አቶ ሃይለሚካኤል አየለ እንደገለጹት የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የደን ተከላ ሥራዎች አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እንዳትጋለጥና የድርቅና የጎርፍ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ።
ዘንደሮ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ የስነ አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራት 167 በመቶ መተግበር ተችሏል ብለዋል ፡፡
በህዝብ ንቅናቄ ስራው ላይ ከስልጠና ጀምሮ በቂ ዝግጅት በመደረጉ ከእቅድ በላይ ማከናወን መቻሉን ነው የጠቆሙት ፡፡
በህዝብ ንቅናቄ በ6 ሽህ 706 ተፋሰሶች ላይ በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከ19 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡
ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተጎዳና ቦረቦር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከላከል መልሰው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንም እንዲሁ፡፡
ህብረተሰቡን ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው ተጠቃሚ ለማድረግ 200 ሽህ መሬት አልባ ወጣቶችና ሴቶችን በማደራጀት ያገገሙ ተፋሰሶችን አልምተው እንዲጠቀሙ እቅድ መያዙም ተጠቁሟል፡፡
በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ ተራሮች አገግመዋል ፤ጠፍተው የነበሩ እጽዋትም እንደገና በመታየታቸው የአካባቢያቸው ልምላሜ መመለሱን ነው ያስታወሱት-(ኢዜአ) ፡፡