ዩኤስ ኤድ 18ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የወተት ማምረቻ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ( ዩኤስ ኤድ) 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የወተትና የወተት  ግብዓት ማምረቻ ቁሳቁሶችን ለአራት  ክልሎች  በድጋፍ  መልክ አበረከተ  ።

ዩኤስ ኤድ ድጋፉን ያደረገው  በአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ  በሺዎች  ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች   የተሻለ  ጥራት  ያላቸው  የወተትና የወተት  ግብዓት  ምርቶችን  ለገበያ  እንዲያቀርቡ  የሚያስችል  ነው ብለዋል ።

በድጋፍ  የተሠጡት  ቁሳቁሶች የወተት ማሸጊያ  ፣ የወተት ማለቢያ ፣ ማቀዝቀዣ፣ ማከማቻ ፣ የወተት  ማቆያ፣ መፈተሻና  ማሞቂያ ማሽኖች  መሆናቸው   ተገልጿል ።  

የዩኤስ ኤድ የልማት ተልዕኮ ዳይሬክተር  ሌሊሴ ሪድ ድጋፍ  የተደረጉትን ቁሳቁሶች  የተለያዩ   የፌደራል መንግሥት ተወካዮች ፣ የክልል ቢሮ  ኃላፊዎችና  አጋር ድርጅቶች  በተገኙበት  ለእንስሳትና አሳ ሃብት ሚንስትር  ለሆኑት  ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ አስረክበዋል ።

የቁሳቁስ ድጋፉን  አስመልክተው የዩኤስኤድ ዳይሬክተር የሆኑት  ሌሊሴ ሪድ እንደተናገሩት “ የእንስሳት ዘርፉን  የተሻለና  ትርፋማ  ለማድረግ የሚመለከታቸው  አካላት  በሙሉ በጋራ ተባባረው መሥራት ከቻሉ  በዘርፉ ላይ የተሠማሩትን  አርሶ አደሮች  ተጠቃሚ  ከማድረግ ባሻገር ዘርፉ  ለአገር ምጣኔ  ሃብትም ትልቅ  አስተዋጽኦ ያበረክታል ”ብለዋል ።

በቀጣይም ዘርፉን ለመደገፍ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በእንስሳትና የወተት ልማት  ከተሠማሩ አካላት ጋር ተባባረው እንደሚሠሩና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ  አረጋግጠዋል ።   

ዩኤስኤድ  በኢትዮጵያ  የእንስሳት  ሃብት  ዘረፉን  ለማሳደግ  በሁለተኛው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተቀመጠው  ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ድጋፎችን  በማድረግ ላይ ይገኛል ።