ጨፌ ኦሮሚያ ከ63 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበውን የ2011 በጀት አፀደቀ

ጨፌ ኦሮሚያ ከ63 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2011 የኦሮሚያ ክልል የመንግስት በጀት አፀደቀ።

ጨፌው  በሦስተኛው  ቀን  ስብሰባው 63 ቢሊየን 440 ሚሊየን 979 ሺህ 580 ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2011 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጀትን አፅድቋል።

ከበጀቱ ውስጥ ከ12 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ብሩ ለተዘዋዋሪ ፈንድ የሚውል ይሆናል።

ከተመደበው አጠቀላይ  ገንዘብ የ14 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ  የሚሆነው  ለካፒታል በጀት የተመደበ ነው።

ከአጠቃላይ  በጀቱ 36 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ደግሞ ለወረዳና ከተሞች ድጋፍ የሚውል ሲሆን፥ 500 ሚሊየን ብር ተጠባባቂ በጀት እንዲሆን አጽድቆታል።

በተጨማሪም የክልሉን ኦዲት ቢሮ የ2011 በጀት እቅድ እና የጨፌ ኦሮሚያ ፅህፈት ቤት ሪፖርትን  ሰምቶ   ውይይት  ካካሄደ  በኋላ አፅድቆታል።

ጨፌው በተያዘው አመት ሊካሄድ የነበረው የወረዳ፣ ከተማ እና የቀበሌ ምርጫም ካለው ሁኔታ አንጻር አመች ባለመሆኑና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲያስችል በቀጣዩ አመት እንዲካሄድም ወስኗል።

ከዚህ ባለፈም በተለያየ ምክንያት መሥራት ያልቻሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን የሚተኩ ሰዎችንም ሾሟል ።(ኤፍቢሲ)