የተፋሰስ ልማትና የአፈር እቀባ ስራዎች ከጎርፍና ተያያዥ ስጋቶች እንዲላቀቁ እያደረገ ነው – የደሴና ድሬዳዋ ነዋሪዎች

የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ባከናወኗቸው የተፋሰስ ልማትና የአፈር እቀባ ስራዎች ተራሮቹ እንዲያገግሙ በማድረጋቸው ሰርተው ከመጠቀም ባለፈ ከጎርፍና ተያያዥ ስጋቶች እየተላቀቁ መሆናቸውን በከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም የአካባቢ ልማት ተሳትፎ ተጠቃሚ የሆኑ የደሴ እና ድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ባለፉት ጊዜያት በአካባቢያቸው በሚከሰተው ጎርፍ የሰው ህይወት መቀማትን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰባቸው መቆየቱን አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በተራሮች መሃል የከተሙት ድሬዳዋ እና ደሴ በመልከዓምድራዊ አቀማመጣቸው በፈጠረው የጎርፍ ተጋላጭነት ምክንያት ዋጋ ሲከፍሉ እንደቆዩ የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎርፍ ስጋት ለመላቀቅ እና ተያያዥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በስፋት እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም የአካባቢ ልማት ተጠቃሚ ዜጎችም ከሚሰማሩባቸው የከተማ ልማት ተግባራት መካከል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና አፈር እቀባ ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የየከተሞቹ የስራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስተባባሪዎች  ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የተሳተፉ ተጠቃሚዎች በከተሞች ልማት በተለይም በተፋሰስ ልማት ስራው እያስመዘገቡ የመጡት ስኬት በአብዛኞች ዘንድ ሰርጾ የኖረው በከተሞች እንዲህ ዓይነት ስራዎች የአይቻሉም መንፈስ የተሰበረበት፣ አበረታች ልምዶችና ተመክሮዎች ያገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡