የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የክልሉን በጀትና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የክልሉን በጀትና የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ የክልሉን የ2011 በጀት ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ከተመደበው በጀት 2 ቢሊዮን 385 ሚሊዮን የሚሆነው ከፌደራል መንግስት በድጎማ የሚገኝ ነው።

ከክልሉ የተለያየ ገቢ የሚሰበሰበው 889 ሚሊዮን 712 ሺህ ብር ሲሆን ቀሪው ከውጪ እርዳታና ከሌሎች ምንጮች የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከጠቅላላው በጀት ውስጥም ለክልል መሥሪያ ቤቶች 1 ቢሊዮን 346 ሚሊዮን የተመደበ ሲሆን ለወረዳዎች ደግሞ 1 ቢሊዮን 973 ሚሊዮን መመደቡን ተናግረዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ፍሬህይወት ገለጻ ለመደበኛና ለካፒታል የተመደበው ገንዘብ 1 ቢሊዮን 346 ሚሊዮን ብር ሲሆን ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበው ደግሞ 109 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ለመጠባበቂያ 15 ሚሊዮን ብር ቀሪው ለልዩ ለዩ ወጪዎች መመደቡን አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የክልሉ በጀት ላይ ከተወያዩ በኋላ በሙሉ ድምጽ ተቀብለው አጽድቀዋል፡

ከእዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን የቀረበውን የስምንት የካቢኔ አባላት ሹመትና ሽግሽግ ተቀብሎ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ከካቢኔ አበላት በተጨማሪ ስድስት የክልሉ ጠቅላይና የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ በላይ ወድሻ በበኩላቸው በጀትን በአግባቡ መጠቀምና ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሙለታ ወምበር እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የልማት ጥያቄን ለመመለስ በድጎማ የሚገኘውን የክልሉን በጀት በክልሉ የውስጥ ገቢ መተካት ተገቢ መሆኑን አስገንዝዋል፡፡ (ኢዜአ)