በነሐሴ ወር የነዳጅ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል-ንግድ ሚኒስቴር

በነሐሴ ወር የነዳጅ ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥል የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከነሐሴ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎች ነዳጅ ምርቶች ዋጋ በሐምሌ ወር ባለው የመሸጫ ዋጋ ይቀጥላል።

የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ግን በሐምሌ ወር ሲሸጥበት ከነበረው በ0 ነጥብ 42 ሳንቲም ቀንሷል።

በመሆኑም በሊትር ብር 24 ከ66 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የአውሮፕላን ነዳጅ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በሊትር 24 ብር ከ24 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዚህ ዓመት ሃምሌ ወር የነዳጅ ምርቶችን በሊትር የገዛበት ዋጋ በነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ጭማሪ ከተደረገበት ከመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ከተገዛበት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

ሆኖም መንግስት የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል በማሰብ ነው ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎች ነዳጅ ምርቶች ዋጋ ባለበት አንዲቀጥል የወሰነው ተብሏል። (ኢዜአ)