ባለስልጣኑ ሁለት አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሁለት አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል፡፡

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ ከደብረብርሀን አንኮበር እና ከኦብሎ ደርሚ የሚሸፍኑ መሆናቸውን ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

ከደብረ ብርሃን አንኮበር የሚደረገው የመንገድ ግንባታ 42 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ለመንገዱ ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ አኳያ አሁን ያለውን የጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ኮንክሪት በማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

መንገዱም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በሳንሻይን ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው ከኦብሎ ደርሚ መንገድ ግንባታ የ69 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከዚህ በፊት የነበረው መንገድ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልነበረ እና በአሁኑ ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ እንደሚሰራ አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡

ይህ መንገድ ደግሞ በክሮስ ላንድ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ በ893 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚገነባም አስታውቋል፡፡

የመንገዶቹ ወጪም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡