የቻይና አፍሪካ ፎረም በቤጂንግ መካሄድ ጀመረ

የቻይና አፍሪካ ፎረም በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በዛሬው እለት መካሄድ የተጀመረው የቻይና አፍሪካ ፎረም ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቻይና ፖሊሲዋን ክፍት ለማድረግ ቁርጠኛ ነች ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ አለመረጋጋቶች ቢስተዋሉም ቻይና ግን እኩል ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የትብብር እድሎችን ክፍት እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የዓለም ኢኮኖሚ ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ እና ለሁሉም ክፍት እንዲሆን ቻይና ዘብ ትቆማለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሌሎችን ማግለል እና ሁሉንም ነገር አንዱ ልጠቅልል ማለትን ግን ትቃወማለች ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አክለውም፥ የቻይና አፍሪካ ትብብር እኩል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እና ስኬታማ ነው ሲሉም አወድሰዋል።

“ቻይና ለአፍሪካ የቅርብ ወዳጅ፣ ተግባራዊ እና ታማኝ ጓደኛ ነች፤ አፍሪካን ሁሌም እንወዳለን፣ እናከብራለን፣ እንደግፋለን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር እና የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በበኩላቸው፥ ቻይና እኩል ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ወዳጅ ነች ብለዋል።

ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት መልካም እና የምንተማመንባት ወዳጅ ሀገር ነች ሲሉም ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ለቻይናው ፕሬዚዳንት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለአፍሪካ ትኩረት ሰጥተው በመስራት አብዛኛውን የአፍሪካ ሀገራት ጎብኝተዋል ብለዋል።

ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፤ በቀጣይ በአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት በሚያደርጉበት ውቅት በታላቅ ክብር አንቀበላቸዋለን ነው ያሉት።

በዛሬው እለት የተጀመረው የቻይና አፍሪካ ፎረም እስከ ነገው እለት ቀጥሎ በመካሄድ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)