የዓለም ገንዘብ ድርጅት ልዑክ የሀገሪቱን ዓመታዊ ኢኮኖሚ ለመገምገም አዲስ አበባ ገባ

የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) ልዑክ የሀገሪቱን የአውሮፓውያኑ የ2018 ዓመታዊ ኢኮኖሚ ግምገማ ለማድረግ አዲስ አበባ ገብቷል።

በሚስተር ጁሊዮ ኤስኮላኖ የሚመራው ይህ ልዑክ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በፊሲካል ፖሊሲ፣ በገንዘብና ፋይናንስ ዘርፍ እና በውጭ ዘርፍ ዙሪያ አፈጻጸሞችን እንደሚገመግም ይጠበቃል።

ቡድኑ በዋናነት በ2010 የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሞችና በቀጣዮቹ ዓመታት ዕይታ ላይ ግምገማ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በመጨረሻው የግምገማው ምዕራፍም የግምገማ ረቂቅ ሪፖርት በማዘጋጀት ለሀገሪቱ ፖሊሲ አውጭዎች እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ልኡኩ በቆይታው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝቶ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ በመለዋወጥ እንደሚመክርም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም ገንዘብ ድርጅት ልኡኩ  በዛሬው እለት ስራውን የጀመረ ሲሆን፥ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም ተከስተ  እና ከብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ጋር ተገናኝቶ ውይይት አድርጓል።

በተጨማሪም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት የሥራ ኃላፊዎችም ጋር በ2010 የፊሲካል ፖሊሲ አፈጻጸምና በ2011 በጀት ላይ የመጀመሪያውን ስብሰባው አካሄዷል፡፡

በቀጣይም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች እና የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከግል ዘርፍ ተቋማትና ከልማት አጋሮች ጋር በሚመለከታቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።