የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጪው መስከረም 27 በይፋ እንደሚመረቅ ተገለጸ

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት እሁድ መስከረም 27 2011 ዓ.ም በይፋ እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርአቱ ላይ ከጠቀላይ ሚኒትሩ በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ግንባታው በ2009 ዓመተ ምህረት ጥቅምት ወር ላይ የተጀመረው ይህ ፓርክ፤ በ102 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ከ147 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ እደተደረገበት ይነገራል፡፡

ፓርኩ በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ኩባንያዎች የሚያገለግሉ 19 የመስሪያ ቦታዎችን የያዘ ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሀገርቷ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ያግዛል የተባሉና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉትን ፓርኮች በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡