የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው – ኢትዮ ቴሌኮም

በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ እያሳጣ ያለውን የቴሌኮም ማጭበርበር ለመከላከል የተቋሙን ደህንነት ኦዲት በማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ።

የቴሌኮም ማጭበርበር በአለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ እና አካሄዱም ተለዋዋጭ እና አደገኛ እየሆነ መጥቷል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአለም አቀፍ ደረጃ በቴሌኮም ማጭበርበር የዘርፉ ኩባንያዎች በአመት 30 ቢሊየን ዶላር ያጣሉ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩም ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኩባንያው በተለይ በአለም አቀፍ ጥሪዎች በሚፈጸም የቴሌኮም ማጭበርበር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የስትራቴጅ እና ፕሮጀከት ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ማህዲ ጀማል ሽኩር በበኩላቸው፥ ተቋሙ ባለፈው አመት ብቻ ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ ተደውሎ በሃገር ውስጥ ቁጥር በሚገባ ጥሪ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማጣቱን ይናገራሉ።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት የቴሌኮም ማጭበርበሩ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከሃገር ውስጥም የሚፈፀም መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ መልኩ የዲጂታል ቴክኖሎጅ በኩባንያዎች ላይ የሚፈፀሙ ማጭበርበሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ሲታዩ፥ በኩባንያው ሰራተኞች የመሆን እድላቸው 85 በመቶ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ይህን መሰል ችግር ለመከላከልም አሁን ላይ ኩባንያው የደህንነት ኦዲት እርምጃ መውሰዱን ጠቅሰው፥ የደህንነት ኦዲት ውጤቱ ግን ብዙ ክፍተት ያለበት ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

የኩባንያው የስትራቴጂ እና ፕሮጀከት ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ማህዲ ጀማል የቴሌኮም ማጭበርበርን የሚመለከተው አዋጅ አሁን ካለው የማጭበርበር አካሄድ ጋር የሚመጣጠን አይደለም ነው የሚሉት።

ለዚህ ደግሞ በቴሌኮም ማጭበርበር ሂደት የሚሳተፉ አካላት ከጊዜው ጋር እየዘመኑና ለዚህ በሚረዳቸው መልኩ እየተሻሻሉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

በዚህም የተነሳ ኢትዮ ቴሌኮም በአዋጁ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል የህግ ክፍሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን ተቋሙ አዳዲስ አገልግሎቶችን ሲጀምር አሰራሩን እየተከተሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያጭበረብሩና ከውስጥም የተቋሙን አገልግሎት ያልተገባ ጥቅም ላይ የሚያውሉ ሰራተኞች መኖራቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ያነሳሉ።

አሁን ላይም በኩባንያው ውስጥ የሚፈፀሙ ማጭበርበሮችን ለመከላከል የአደረጃጀት ማሻሻያ መደረጉን እና የተወሰኑት ለፍትህ አካላት ቀርበው የታገዱ እና ጉዳያቸው በህግ እየታየ ያሉ አካላት መኖራቸውንም አስረድተዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በአለም አቀፍ ጥሪዎች ላይ የሚፈፀመውን ማጭበርበር ለመከላከልም አዲስ ሲስተም ባለፈው አርብ መገጠሙን እና ባለፉት ጥቂት ቀናት ውጤት ማምጣት መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህም ኩባንያው በቀን ከአለም አቀፍ ጥሪዎች ያገኘው የነበረው ገቢ መሻሻሉንም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ኩባንያው ከቴሌኮም ማጭበርበር ራሱን ለመከላከል አዳዲስ ሲስተሞችን እየገጠመና አጥፊዎቹን ለፍርድ እያቀረበ መጓዙን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።(ኤፍቢሲ)