የቁም እንስሳትን ምርት ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ባለሃብቶች የሙያና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ድጋፍ ይደረጋል

 የቁም እንስሳትን ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መንግስት የሙያ እና የፋይናንስ አቅርቦት ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል ተባለ።

ኢትዮጵያ ከቁም እንስሳት ሃብቷ ያላትን ያክል ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም።

ዘርፉ ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢ የ17 በመቶ እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ ከ18 እስከ 19 በመቶ ብቻ ድርሻን ይይዛል።

ለዚህ ደግሞ ከጥራት ይልቅ ቁጥርን መሰረት ያደረገ የእንስሳት ምርት እንቅስቃሴው ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብይትና ግብአት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሰይፉ አሰፋ፥ በዘርፉ ጥራትን ለማምጣት እና ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ጋር እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ።

በሀገሪቱ የወጡት ፖሊሲዎች፣ ፍኖተ ካርታዎች እና አዋጆች በስራ ላይ አለመዋል ለችግሩ መንስኤ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ አሁን ላይ መንግስት በግብርና ሚኒስቴር ስር ትልቅ የግብይት ዘርፍ ማቋቋሙን ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ደግሞ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና እና ዘርፉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አለመመራቱ፥ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም በጥራት ምክንያት የምርት መቀነስ እያጋጠማቸው መሆኑን በመጥቀስ፥ መንግስት ከምንጩ መስራት አለበት ባይ ናቸው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያመች ዘንድ መንግስት በክልሎች በኩል የተለያዩ ስልጠናዎችን ለባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት በመስጠት ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል።

በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመታዊ የስጋ ምርትን ከ94 ሺህ 240 ቶን በላይ ለማድረስ ታቅዷል፤ ይህ ደግሞ ከ374 ሚሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት ይረዳል።

ይህ እንዲሳካና ባለሃብቶች ለሃገር እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ፥ ሙያን ጨምሮ የፋይናንስ ድጋፍ ለባለሃብቶች እንደሚደረግ ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ 2050 የአፍሪካ የስጋ ፍጆታ 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን እንደሚደርስ ይገመታል፤ በዘርፉ መስራት ከተቻለ በአህጉሩ በእንስሳት ሃብቷ ቀዳሚ ለሆነችው ሃገር መልካም አጋጣሚ ይሆናል።(ኤፍ ቢ ሲ)