ለአፍሪካ አገራት ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ሊጀመር ነው

በኢትዮጵያ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ነው።

የመዳረሻ ቪዛው ለአፍሪካ አገራት ዜጎች መሰጠቱ ለአገሪቱ ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ቦጋለ እንደገለጹት፤ ለአፍሪካ አገራት ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል።

ቀደም ሲል ከተለያዩ የዓለም አገራትና ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን ብቻ በማካተት ለ37 አገራት ብቻ አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ አሁን ለሁሉም አፍሪካዊያን ይሰጣል ብለዋል።

በመሆኑም በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉ በሙሉ የአገልግሎት ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ ተደራሽ ለማድረግና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ባለሙያዎችን የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ይኸው የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለአፍሪካ አገራት ዜጎች መሰጠቱ ለአገሪቱ ቱሪዝም ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ደግሞ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአገራቱን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከሩም ባሻገር በሆቴሎች፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች ዕድገት ለማምጣት አስተዋጽዖው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያውና የዓለም አቀፉ የፌር ፋክስ ኩባንያ ሰብሳቢ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደተናገሩት፤ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎቱ ለአፍሪካዊያን መጀመሩ ለቱሪዝም ዕድገት አስተዋጽዖ ያደርጋል።

በተለይም ሁለተኛ በረራቸውን በኢትዮጵያ በኩል የሚያደርጉ ተጓዞች በመቆያ ጊዜያቸው እንዲጎበኙ ዕድል ስለሚሰጥ በተዘዋዋሪ ለአገሪቱ ጥቅም ያስገኛል የሚል እምነት አላቸው።

ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር አሰፋ አድማሴም ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ በመጋራት የአገልግሎቱ መጀመር አፍሪካዊያን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ተነሳሽነት አንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ በተለይም በቱሪዝም በምታገኘው ገቢ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የምታካሂዳቸውን የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ለማበረታታት ያስችላልም ነው ያሉት።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2025 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 18 ሚሊዮን መንገደኞች ለማጓጓዝ ማቀዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። (ምንጭ፡- ኢዜአ)