የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመዘግየትን ችግር ለመፍታት የማሻሻያ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያጋጠመውን የመዘግየት ችግር ለመፍታትና ግንባታውን ለማፋጠን መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችንና የማሻሻዎች ተግባራትን  እያከናወነ እንደሚገኝ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ኢትዮጵያዊያንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ12 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የቦንድ ግዠና ድጋፍ አድርገዋል።

በ2011 የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም 266 ሚሊየን 446ሺ ብር በላይ የሚያወጣ ቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል ብለዋል።  

ከዚህ ውስጥ 3ነጥብ3 ሚሊየን ብር ከዲያስፖራ በቦንድና ልገሳ የተደረገ ድጋፍ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን 2ቢሊየን ብር 243 ሚሊየን ብር በላይ ቦንድ ከነወለዱ ተመላሽ ተደርጓል ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ህብረተሰቡ አሁንም ድጋፉ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጽህፈት ቤቱ  ጠይቋል።