የኦሮሚያ ክልል አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል

የኦሮሚያ ክልል በክልሉ የሚገኘውን  አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን  በማሳደግ  አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ አስታወቀ ፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ ከ6 ቢሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በእርሻ የለማ ሲሆን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ  አሲዳማ እንደሆነ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ በበኩላቸው በክልሉ ከሚገኘው መሬት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው አሲዳማ ሲሆን 20 በመቶው ደግሞ ጨዋማ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በክልሉ ከሚገኘው መሬት አብዛኛው ምርታማ ባለመሆኑ አርሶ አደሩም ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡

ይህን አሲዳማና ምርታማ ያልሆነ መሬት በኖራ በማከም ምርታማ ማድረግ በመቻሉ ክልሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን የኖራ ፋብሪካ አስገንብቶ ለአርሶ አደሩ ኖራን በማሰራጨት መሬቱን በማከም እንዲጠቀሙ ጥረት  በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በዚሁ ዞን በኖራ ቴክኖሎጂ የለማና ምርታማ መሆን የቻለ የአርሶ አደሮች ማሳ መጎብኘቱም ተገልጿል፡፡

የኖራ ፋብሪካው በአመት 35 ሺህ ኩንታል ኖራ የሚያመርት ሲሆን ይህን ተሞክሮ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች የኖራ ፋብሪካ ግንባታ መከናወኑን ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ጠቁመዋል፡፡