ሴቶች ለሰላም መረጋገጥ ከሰሩ በገቢ አሰባሰብ ላይ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጹ

የሴቶች በመሪነት ሚናቸው ለሰላም መረጋገጥ ከሰሩ በገቢ አሰባሰብ ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ሴቶች ሰላምን በማረጋገጥና በገቢ አሰባሰብ ላይ ስለሚኖራቸው ሚና ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር ሴት ሠራተኞች ውይይት አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንዲቻል በቀዳሚነት ሰላም መረጋገጥ ይኖርበታል።

ገቢ በአግባቡ ተሰብስቦ ለህብረተሰብ አገልግሎትና ተጠቃሚነት ካልዋለ በዚያው ልክ ሰላም እንደሚታወክ ነው የተናገሩት።

ሴቶች ሰላምና ገቢ ያላቸውን ተያያዥነት ተረድተው ሰላምን እያስከበሩ ገቢን በታማኝነት፣ ከሙስና በፀዳና በታታሪነት እንዲሰበስብ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

ሴቶች ባሉበት የስራ ዘርፍ ሙስና ልግመኝነት ስፍራ እንዳይኖራቸው የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በመድረኩ የተሳተፉ ሴቶች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ብቃታቸውን በተግባር ለማሳየት እንደሚጥሩ ገልፀው በአሁን ወቅት የሚያጋጥሟቸውን አስተዳደራዊ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገቡ አመልክተዋል።

ተሳታፊዎቹ ከሰጡት አስተያየት፤ ‘በዝቅተኛ የስራ ዘርፍ ላይ ያሉ ሴቶች በተቋሙ እኩል ተጠቃሚ አይደሉም፣ የደረጃ እድገትና ጥቅም ላይ ከወንዶች እኩል እድል እየተሰጠ አይደለም፣ ስነ ምግባር የሌላቸውና በሙስና የተያዙ አመራር አባላት ሴቷን ያለመመሪያ እንዳሻቸው ከቦታ ቦታ እያዛወሩ ነው፣ አቅም ያላቸው ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ አይፈለግም’ የሚሉት ይገኙበታል።

ለተነሱ አስተያየት ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሯ ችግሮቹ በተቋሙ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መልክ ያለው መሆኑን ገልፀው፤ በጋራ ተባብሮ በመታገል መፍታት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ አግባብ ባልሆነ መልኩ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ የሚጎዱ ነገሮች መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

መድረኩ ጀግኒት በሚል የተጀመረ የሴቶች የንቅናቄ መድረክ አንድ አካል ነው። (ኢዜአ)