ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ለገሃር የሚገነባውን የተቀናጀ የመኖርያ መንደር ስራ አስጀመሩ

በአዲስ አበባ ከተማ በተባበሩት አረብ ኢሚሬት ኩባንያ አማካኝነት በ36 ሄክታር መሬት ላይ  ግንባታው የሚከናወነው የትንሽ ከተማ  ምሥረታ ፕሮጀክት  በዛሬው ዕለት  በይፋ  እንዲጀመር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድና  የኩባንያዉ ተወካይ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት ተወካዮችና ኩባንያዎች  በተገኙበት በዛሬው ዕለት  በ36  ሄክታር  መሬት ላይ የሚካሄደው  የትንሽ ከተማ  ግንባታ ፕሮጀክት  ይፋ ተደርጓል ።

ፕሮጀክቱ  በውስጡ ሆቴሎች ፣ የአረንጓዴ ሥፍራ ፣ የመናፈሻ ቦታዎችና  የተለያዩ  የገበያ ማዕከላትን የሚያሟላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሜክሲኮ  ወደ  ቄራ  በሚወስደው  መንገድ  ላይ  የቀድሞ የኢትዮ-ጅቡቲ  የባቡር ጣቢያ ግቢን  የሚያካትት መሆኑ  ተገልጿል ።

በተጨማሪም በለገሃር አካባቢ የሚገኙትን የጉምሩክ መጋዘኖችን ግቢ ለፕሮጀክቱ እንደሚያውል  ተመልክቷል ።

ተግባራዊ  በሚደረግበት አካባቢ  የሚገኙ 1ሺ 500 የሚደርሱ  ነዋሪዎችም  በፕሮጀክቱ  ውስጥ  ተካተው  ከአካባቢያቸው ሳይነሱ  ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታም መመቻቸቱም ተገልጿል ።

ዶክተር አብይ አህመድ ወደ  ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተባባሩት አረብ ኢምሬትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው  ግንኙነት  እየተጠናከረ በመምጣቱ  የተባባሩት ኢሚሬቶች  በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ  ለመሳተፍ ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል ።