የአለም ባንክ ለብርሃን ለሁሉም ፕሮግራም 375 ሚሊየን ዶላር ፈቀደ

የአለም ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወነው ብርሃን ለሁሉም ፕሮግራም 375 ሚሊየን ዶላር መፍቀዱን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት  ባንኩ ከፈቀደው ገንዘብ ለሥራ ማስጀመሪያነት የሚሆን 60 ሚሊየን ዶላር በአሁኑ ወቅት ተለቋል።

በአሁን ወቅትም  የሀገሪቱ  የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት  አቅም በዓመት  4 ሺህ 200 ሜጋ ዋት መሆኑን መድረሱም  ተገልጿል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ እና የሀገሪቱ ህዝብን መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መርሃ ግብር ባለፈው  ዓመት በ2010 ዓም ጥቅምት ወር ላይ ይፋ መደረጉ ይታወሳል ።

ባለፈው አመት ይፋ የተደረገው ይህ የብርሀን ለሁሉም ወይም የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ከሰባት እስከ ስምንት አመት ጊዜን የሚወስድ ነው ተብሏል።

ይህም በተወሰነ የጊዜ ገደብ ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንና መርሀ ግብሩ ሁሉንም ሀብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግም የራሱ አሰራርን እንዳስቀመጠም ተገልጿል።

አቶ ብዙነህ በዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ከሚሆኑት ወይም አሁን ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከማያገኙት 65 ከመቶ ያህሉን ከብሄራዊ የኤሌከተሪክ ቋት አገለግሎት እንዲያገኙ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።

35 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሶላር እና ሌሎች ታዳሽ ኃይሎችን በመጠቀም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል የፕሮግራሙ አካል እንደሆነ ተነግሯል።

የብርሀን ለሁሉም ፕሮግራም የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ታውቋል።

የዚህን ፕሮግራም ሀገሪቱ የተወሰነውን ወጪ የምትሽፍን ቢሆንም ከተለያዩ ሀገራት ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አቶ ብዙነህ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአለም ባንክ ለፕሮግራሙ ማስጀመሪያ 375 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ስምምነት ከተደረሰበት ውስጥ 60 ሚሊየን ዶላሩ መለቀቁን የተናገሩት  ዳይሬክተሩ ከሌሎች ድጋፍ ሠጭ ሀገራትም ገንዘብ ለመፍቀድ ፍላጎት እያሳዩ ነው ብለዋል።

ፍላጎት ካሳዩት ውስጥም የአፍሪካ ልማት ባንክ እንደሚገኝበትም ጠቅሰዋል አቶ ብዙነህ ቶልቻ።

ፕሮግራሙን ወደ መሬት ለማውረድ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግም በአሁኑ ሰአት ገንዘብ ከማፈላለግ በተጨማሪ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል።

በዚህም ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያስፈልጉ እቃዎችን ግዥ መፈፀም እና ቀድመው የተገዙ  ግብአቶችን ወደ ክልሎች የማሰራጨት ስራ እንደሚገኝበት ተጠቁሟል።

እንዲሁም በክልሎች ስራዎች የሚከናወኑባቸው ሳይቶችን የመለየት ስራ መከናወኑን ነው አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።

በብሄራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ተደራሽ ከሚሆኑት ውጭ ለሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም ክልሎች ወደ 240 የሚደርሱ ቦታዎች ተለይተዋል።

ፕሮግራሙ በተያዘለት እቅድ ተግባራዊ አልተደረገም ያሉት ዳይሬክተሩ  እስካሁን ያልጀመረው  በአቅም ማነስ  እና በሌሎች ጉዳዮች ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በአሁን ወቅት የፕሮግራሙን ስራ በአግባቡ እንዲከናወን ክትትል የሚያደርግ ፅህፈት ቤት ሚኒስቴሩ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የመርሀ ግብሩን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እስከ ጥር ድረስ በማጠናቀቅ ከጥር በኋላ ባሉት ሁለት እና ሶስት ወራት ውስጥ ወደ ትግበራ ለመግባት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

መርሀ ግብሩ ሲጠናቀቅም የሀገሪቱን የሀይል ሽፋን  አሁን ካለበት 58 ነጥብ 13 ከፍ ወደ አለ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)