ኢትዮጵያና ዓለም ባንክ የ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራና ለዜጎች የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት የሚውል የ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጠ።

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ ናቸው።

በስምምነቱ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ ብድሩ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እያከናወነች ላለችው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ብድሩ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚለሙ አካባቢዎችን ከማሳደግ ባለፈ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን ችግር በመቀነስ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ትልቅ ሚና አለው።

ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃውን ለማጠናከርና የዜጎችን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት ፕሮግራምና እቅዶችን አውጥታ እየሰራች ሲሆን ዛሬ የዓለም ባንክ ያደረገው ድጋፍ ይህንን ለማጠናከር ይረዳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ብድሩም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ 645 ሺህ አባ ወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው።

የአለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ የምታከናውነውን ተግባር አድንቀው ባንኩ ይህን ለማጠናከር የሚያስችል ብድር ሰጥቷል ነው ያሉት።

ብድሩ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የአየር ብክለትን ለመከላከል ተግባራዊ የሚደረጉ ስራዎችን ለማገዝና በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን  ለማጠናከር የሚረዳ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመከላከል፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ለማከናወን በምታደርገው ጥረት የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል። (ኢዜአ)