በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 64 ሺህ ዶላር፣ 56 ሽጉጦችና 302 የሞባይል ቀፎዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

ባለፉት ሁለት ቀናት በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 64 ሺህ ዶላር፣ 56 ሽጉጦችንና 302 የሞባይል ቀፎዎች በምስራቅ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ቁጥጥር ጣቢያዎች መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በሚኒስቴሩ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ እንደተናገሩት ባለፈው አርብ ዕለት ቶጎ ጫሌ በተባለ ስፍራ ንግስቲ ገብረእግዚአብሄር የተባለች ተጠርጣሪ 64 ሺህ 50 ዶላር ደብቃ ወደ ውጭ ለማሸሽ ስትሞከር ተይዛለች።

በተመሳሳይ ዕለት አቶ ገብረሕይወት ትኩሴና ዘሚካኤል ገብረሕይወት የተባሉ ተጠርጣሪዎች በታርጋ ቁጥር 96035 ኮድ-3 አዲስ አበባ ተሽከርካሪ 302 ሞባይል ቀፎዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞክሩ ተይዘዋል ብለዋል።

በቅዳሜ ዕለት ደግሞ ሙክታር አህመድ ጀማልና ታጁ ሙሃመድ አሊ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በታርጋ ቁጥር 40358 ኮድ-3 ኦሮሚያ በሆነ ተሽከርካሪ አል-በረከቴ በተባለ ስፍራ 56 ሽጉጦች በጉምሩክ ሠራተኞች መያዛቸውን ተናግረዋል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጉምሩክ ቁጥጥር ሥርዓቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት አቶ አዲሱ ህብረተሰቡ አገር የሚበጠብጡትንና ህገ ወጥ ደርጊቶችን በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በሳምንቱ ውስጥ በአዳማ ከተማ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 10ሺህ 200 የአሜሪካን ዶላር ሕብረተሰቡ ባደረገው ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል። (ኢዜአ)