የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጓደል ለነዳጅ እጥረት መንስኤ ነው ተባለ

በሀገሪቱ እየተስተዋለ ላለው የነዳጅ እጥረት የዘርፉ ባለቤትና ተቆጣጣሪዎች መብዛት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጓደል ለችግሩ መንስኤ መሆኑን የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዳዲስ የአደረጃጀት መዋቅርን ይፋ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ አከፋፋዮች፣ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች፣ የማዲያ ባለቤቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት የተገኙበት የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን የውይይቱ ተሣታፊዎች የዘርፉ ችግር ነው ያሏቸውን ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰቷቸዋል፡፡

በአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎትና አቅርቦት ያለመመጣጠን፣ መንግስት በቂ የሆነ ዲፖ አለመኖር፣ የዘርፉ ባለቤት አልባ መሆን፣ የነዳጅ ክፍፍል ፍትሓዊነት መጓደል፣ ከጂቡቲ ወደብ እስከ መሀል ሀገር ከ100 ኪሎሜትር በላይ የመንገድ ችግር መኖር እንዲሁም ህገወጥ የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ መኖር ለሥራዎቻቸው ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን የውይይቱ ተሣታፊዎች አንስተዋል፡፡

የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ወርቁ በበኩላቸው ተሣታፊዎች ያነሱት ችግሮች እንዳሉ በማመን የነዳጅ እጥረትን በአጭር ጊዜ ለመፍታት በተለይም የቢንዚል እጥረት ለአጭር ጊዜ የተፈጠረና አሁን የተፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ በአዲስ አደረጃጀት ለመዘርጋት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡