አስተዳደሩ በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሠጥቼ እየሠራው ነው አለ

የአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር በከተማዋ የተጀመሩ  የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት  ለማጠናቀቅ  ትኩረት ሠጥቶ  እየሠራ  መሆኑን  አስታወቀ ።

የአዲስ  አበባ ከተማ  ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በየካ ክፍለ ከተማ የተጠናቀቁ  የልማት  ሥራዎችን  በዛሬው ዕለት አስመርቀዋል ።

በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት ተጀምረው ግንባታቸው  የተጓተቱ  ፕሮጀክቶች  በፍጥነትና የጥራት  ደረጃቸው ተጠብቆ  እንዲጠናቀቁ  ትኩረት  ተሠጥቶ እየተሠራ  መሆኑን  ምክትል ከንቲባው  ተናግረዋል ።

በዛሬው  ዕለት በተካሄደው  ሥነ ሥርዓት ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ  ትምህርት ቤቶች ፣ ጤና  ጣቢያዎች ፣ መንገዶችና የጥቃቅንና አነስተኛ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች  ተመርቀዋል ።

አስተዳደሩ ያስመረቃቸው የልማት ተቋማቱ የመብራት ፣ የውስጥ መንገዶችና  የውሃ  አገልግሎቶች  እንዲሟሉላቸው  ከተደረገ በኋላ መመረቃቸውን  ተገልጿል ።

ከዚህ በፊት የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በፍጥነት የማጠናቀቅና አዲስ የተጀመሩትን  ፕሮጀክቶች  በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ  ከመቼውም  ጊዜ  በላይ  በትኩረት  እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል  ከንቲባው ተናግረዋል ።