“ግብር ከፋዮች ለሀገርና ለወገን ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት የግብር አከፋፈል ኃላፊነትና ስነ-ልቦና ማጎልበት ያስፈልጋቸዋል” ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በገቢዎች ሚኒስቴር በተዘጋጀዉነና  “ግዴታየን እወጣለሁ፤ መብቴንም እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ የገቢ ንቅናቄ የመክፈቻ ሥነ – ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ገቢ ለአገር እድገትና ስልጣኔ ዋነኛ መሰረት መሆኑን ገልፀዉ  “ግብር ከፋዮች ለሀገርና ለወገን ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት የግብር አከፋፈል ኃላፊነትና ስነ-ልቦና ማጎልበት ያስፈልጋል” ብለዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግብር ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ ስርዓት እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸዉ እንደገለፁት ይህ መርሃ ግብር  የተዘጋጀው ትክክለኛ የታክስ ገቢ ማሰባሰብ ስርዓትን ለመዘርጋትና ህገወጥነትን ለመግታት ነው።

የሀገሪቱን የውሃ፤ የኢነርጂ፤ የትምህርት፤የጤና እና የመስኖ ልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ከዚህም 75 በመቶ የሚሆነው ከገቢ ታክስ ሊሰበሰብ መታቀዱም ተገልጿል።

በዚህም መሰረት እስከ መጪው አንድ ዓመት ድረስ አገር አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ ውይይቶችና ሌሎች መድረኮች ይዘጋጃሉ።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።