በከተማ አስተዳደሩ ለረጅም ጊዜ ሳይለማ የቆየና የመንግስት ልማት ድርጅቶች የሆነ ከ10 ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደረገ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ ሳይለማ የቆየ እና ባለቤትነቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የሆነ 10 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ማድረጉን ገለጸ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በግል እና በመንግስት የልማት ድርጅት ባለቤትነት ለረዥም ጊዜ ተይዘው ሳይለሙ የቆዩ ቦታዎችን ወደ መንግስት ይዞታ የመመለስ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ነው የከንቲባው ጽህፈት ቤት ያስታወቀው፡፡

በትላንትናው ዕለትም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎተራ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚገኙ ሁለት ሰፋፊ ይዞታዎች ማለትም ወደ መሬት ባንክ መመለሱን አስታውቋል፡፡

ወደ መሬት ባንክ የተመለሱ ይዞታዎችም የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ንብረት የሆነውን መጋዘን፣ የሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ክለብ የተጫዋቾች የመኖሪያ ካምፕ እና ተጨማሪ ትርፍ ቦታ በጠቅላላ 97 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ንብረት የነበረው 4 ሺህ 851 ካሬ ሜትር ቦታ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የተመለሱ መሬቶችን የሊዝ አዋጁ በሚደነግገው መንገድ ይዞታዎቹን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ማኔጅመንት ቢሮ ለማስተላለፍ ከስምምነት ላይ መደረሱንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)