የፕሮጀክቶችን የአስተዳደርና አመራር ደረጃን በማስጠበቅ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ከብክነት ማዳን እንደሚቻል ተገለጸ

በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓት ተግባራዊ ቢደረግ በአምስት ዓመታት ውስጥ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከብክነት መታደግ እንደሚቻል የብሄራዊ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በተገኙበት በዛሬው ዕለት የመንግስትና የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ሥርዓት ደንብ ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም በመንግስት ልማት ድርጅቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በስኳር፣ በባቡር፣ በማዳበሪ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጊዜና ገንዘብ ወጪ መናር እንደሚስተዋል ተነስቷል፡፡  

በዚህም የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች ከ60 እስከ 160 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ በጀት እንደሚወጣባቸውም ተገልጿል፡፡

በዛሬው ዕለት ለውይይት የቀረቡ የመንግስት ልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ ደንብና የህግ ማዕቀፍ መነሻ ሐሳቦች በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊ ሆነው በመገኘታቸው ነው ለውይይት የቀረቡት፡፡

የህግ ማዕቀፉ መነሻ ሐሳብ የፌደራል መንግስት ልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራርም ምን መምሰል አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶቹ ጽንሰ ሐሳብ አነሳስና የፕሮጀክቶቹ ልየታ ሂደት እንዲሁም አሰራር ያለበትን ደረጃ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም ረቂቅ ደንቡ የያዛቸውና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ተብለው የታመነባቸው ሐሳቦችን አካቷል፡፡

በመንግስት ፕሮጀክቶች ወጪና ሂደት የተለያዩ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላት ያላቸውን ስልጣንና ኃላፊነት በግልጽ በማስቀመጥ ተጠያቂነትን ግልጸኝነትን በማስፈን የመንግስት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ወጪ ተፈጻሚ የሚሆኑበትትን ስርዓት አስቀምጧል፡፡

ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ሰነዱ ለጠቅላይ አቃቢህግ ይመራል እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ (ኤፍቢሲ)