የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጣሊያን ባለሃብቶች ጋር በሮም ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የጣሊያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በስፋት መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ጥረት  እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ የጣሊያኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ አሥር የሀገሪቱ ባለሃብቶች በተገኙበት ባደረጉት ገለፃ ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የኢንቨስትመንት ሥራውን የሚያከናውነው የሴንተቲክ ጨርቃ ጨርቅ የካርቪኮ ግሩፕ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ላውራ በውይይቱ ተገኝተው ኢንቨስትመንታቸውን አስመልክተው ተሞክሯቸውን ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡  

ካርቪኮ ግሩፕ በአሁኑ ሰዓት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ23 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታውን እያጠናቀቀ ሲሆን፥ በጣሊያንና በቬትናም በሚገኙ ፋብሪካዎች የሰራተኛ ስልጠና በማድረግ ዝግጅቱን ለመጀመር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በውይይቱ የተገኙት ሌሎች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በመድሓኒት፣ በግንባታ፣ በግብርና ማቀነባበርያ እና በአልባሳት ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡( ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)