ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ውይይት አደረጉ

ጠቅላይ ሚንስትር  ዐቢይ አህመድ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ለኢትዮጵያ በሚያደርገው ድጋፍ ዙሪያ ከድርጅቱ መሪ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በጣሊያን ሮም የሚያደርጉትን የልማት አጋሮች ውይይት በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ድ ሲልቫ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ እየተጫወተች ያለውን ሚና አድንቀው በተለይም ሰላም ዋነኛ ቅድመ-ሁኔታ በመሆኑ በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶችን መልካም ጅምሮች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ ለትብብርና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ቅድሚያ እንደሚሰጡ ለዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው የቀጠናው ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የምግብ ዋስትናንና ግብርናን በተመለከተ አገሪቱ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብሯን ስኬታማ ለማድረግ የአነስተኛ ገበሬዎች ዋና ፍላጎት የገበያ ትስስር መሆኑን ዶክተር አብይ ተናግረዋል፡፡

የአለም አቀፉ ምግብና እርሻ ድርጅትም ከኢትዮጵያ ጋር በዚሁ ዙሪያ በሚሰጠው የተቀናጀ የቴክኒክ ድጋፍ ላይና በሌሎችም መስኮች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)