የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አዋጅን አፀደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አዋጅን አፅድቋል፡፡

የጸደቀው አዋጅ የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የአፍሪካ ህብረት አባል አገራትን በኢኮኖሚ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር፣ ሰፊ የገበያ እድሎችን የሚፈጥር ከሌሎች አህጉራት የንግድ ህብረት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችል በዉይይቱ ወቅት ተገልጿል።

ይህ የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ከ49 በላይ አገራት የፈረሙት ሲሆን ይህም የህብረቱ አባል አገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።

እስካሁን 21 አባል አገራት አዋጁን ያፀደቁት ሲሆን 22 አገራት ሲያፀድቁት ወደ ስራ ይገባል ተብሏል።

ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ ከምትልካቸው 30 በመቶ በላይ መዳረሻ የአፍሪካ አገራት በመሆናቸዉ ስምምነቱ ከመስራች ፈራሚ አገራት ጋር ቀዳሚ ሆና ማፅደቋ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን ተገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት በአውሮፓውያኑ 2011 ባወጣው የትግበራ አቅጣጫ መሰረት ይህ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት በቀጣዮቹ አስርት አመታት በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚካሄደውን የንግድ ግንኙነት ከ25 እስከ 30 በመቶ ያሳድጋል ነው የተባለው።