በጋምቤላ ክልል ከ654 ሚሊየን ብር በላይ ብድር የተወሰደባቸው 36 ፕሮጀክቶች በቦታቸው የሉም

በጋምቤላ ክልል ከ654 ሚሊየን ብር በላይ ብደር የተወሰደባቸው 36 የእርሻ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ሳይገቡ መጥፋታቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኮሚቴው አባላት በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት በጋምቤላ ወረዳ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

ባለፉት አመታት የመንግስትን የልማት አቅጣጫ ትኩረት በመከተል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእርሻ ዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች በተለይም ለሰፋፊ በዝናብ በሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና የቴክኒክ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲቋቋሙ የፋይናስ እገዛ ማድረጉ ይነገራል።

በዚህም ባንኩ በፈረንጆቹ 2010/2011 ዓ.ም ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ለ189 በዝናብ የሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ማቋቋሚያና ማልሚያ የሚሆን የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የረጅም ጊዜ ብድር ፈቅዷል።

ይህንን ተከትሎም ቡድኑ በጋምቤላ ወረዳ የሚገኙ 6 ሳይቶችን የተመለከተ ሲሆን፥ ከስድስቱ መካከል ሁለቱ በትክክል ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ታዝቧል።

ቀሪዎቹ ግን ስራቸውን በትክክል እንዳልሰሩ ኮሚቴው የታዘበ ሲሆን፥ አንድ ባለሃብት በራሱ ስም፣ በባለቤቱና በልጁ ስም 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ወስዶ ወደ ስራ እንዳልገባ አረጋግጧል።

ባለሃብቶች መሬቱን ከተረከቡ በኋላ የምንጣሮ ስራ ሰርተው ጥለው እየጠፉ እንደሆነና መሬቱ ለታለመለት አላማ አለመዋሉን ተመልከቷል።

ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ትልልቅ ዛፎች ያለ አግባብ መመንጠራቸው በአካባቢው ማህበረሰብም ቅሬታ እንደፈጠረ የተገለፀ ሲሆን፥ በክልሉ ላይ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እያስከተለ እንደሚገኝም የክልሉ አመራሮች ተናግረዋል።

ቡድኑ ባደረገው ምልከታ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች 20 ሲሆኑ፥ ያለባቸው ብድር 323 ሚሊየን 832 ሺህ 195 ብር ነው።

የተለያዩ ድክመቶች ያሉባቸው ፕሮጀክቶች 133 ሲሆኑ፥ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር 
ብድር እንዳለባቸው ቡድኑ በምልከታው አረጋግጧል።

እንዲሁም እርሻቸውን ጥለው የጠፉ ፕሮጀክቶች ብዛት 36 ሲሆኑ፥ 654 ሚሊየን 320 ሺህ 044 ብር እንደተበደሩ ቡድኑ ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የብድር ሁኔታ ትንተና መሰረት ብዛታቸው 117 የሆኑ ፕሮጀክቶች የብድር አመላለስ ሁኔታቸው አጠራጣሪ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የያዙትም የብድር ገንዘብ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል 44 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በኪሳራ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ የያዙትየብድር ገንዘብ ብዛት 902 ሚሊየን 779 ሺህ 464 ብር መሆኑ ተነግሯል።

የቡድኑ አባላትም ፕሮጀክቶቹ እያጋጠማቸው ያለውን ውስንነት ተረድቶ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ከተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ከተውጣጡ ባለሃብቶች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የቡድኑ አባላትም ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ በቂ የሆነ የገበያ ትስስር መፈጠር አለመቻሉ፣ የተጠናከረ የክትትልና ድጋፍ ስራ አለመሰራቱ እንዲሁም ያመረቱትን ምርት በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ እንደሆነ ባለሀብቶች ለቡድኑ ተናግረዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ኦኬሎ በበኩላቸው በብድር መልክ የተሰጠው ገንዘብ ለታለመለት አላማ ሳይውል ገንዘቡን የወሰዱት ሰዎች በሪል ስቴትና በሆቴል ግንባታ ላይ እንደተሰማሩ ገልጸው፥ ባለሃብቶቹን ለመያዝ ክልሉ ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡  ምንጭ ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ