የምስራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

የምስራቅ አፍሪካ የኢነርጂ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የተዘጋጀውን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ መርሃ ግብር ሁለት ይፋ አድርጋለች።

መርሃ ግብሩ በፈረንጆቹ 2017 የተጀመረና አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሻሽሎ የቀረበ ሲሆን፥ በ2025 ሃገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

መድረኩ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በዓለም ባንክ ትብብር  የተዘጋጀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተጨማሪ ግብዓቶችን የሚታገኝበት እንደሚሆን የተገለጸው፡፡

ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም ሁለት ውስጥ መንግሥት ባለፈው ዓመት የተከናወኑ ሥራዎችን በመዘርዘር ወቅታዊ መረጃዎችን እንደሚያቀርብም ተገልጿል።

በተጨማሪም ከዋናው ግሪድ እና ከግሪድ ውጭ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በጥምረት የሚያሳይ ሲሆን፥ በፐብሊኩና በግሉ ዘርፍ ጥረት በ2025 ከግሪድ ውጭ ያለውን የኤሌክትሪክ ሽፋን በ35 በመቶ ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ተጠቅሷል።

ከዋናው ግሪድ ውጭ ያሉ ቴክኖሎጅዎችን ለማሳደግ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት በጋራ 12 አነስተኛ የግሪድ የሙከራ ስራዎችን በመላ ሀገሪቱ ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰሩ ይገኛል ተብሏል።

ከዘርፉ አመራሮች እና አለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር የሚደረገው ውይይት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያን፣ የጀኔሬሽን እና የስርጭት እንዲሁም የተቋማዊ የአፈጻጸም ማሻሻያ ላይ ያተኩራል።

የምስራቅ አፍሪካ የፕሮግራም አስተባባሪ ካርሚን ቶሩነስ ኢትዮጵያ በኢነርጂው ዘርፍ እየወሰደች ያለው እርምጃ በዘርፉ ላይ ለሚሰሩ እና መሳተፍ ለሚፈልጉ አካላት ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አስተባባሪው ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ሰፊ ህዝብ ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ይዛ የቀረበች መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ከአፍሪካ እና ከዓለም ሀገራት የመጡ የኢነርጂ ሚኒስትሮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አለምአቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶችና የኃይል አመንጪ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡