በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረገ ይገኛል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ለመሳተፍ ቻይና የሚገኘው በጠቅላይ ሚስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራዉ የኢትዮጵያ ልዑክ የተለያዩ ስምምነቶችን እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በቻይና በሚካሄደው የ2ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲብ ጉባኤ፣ በዘንድሮው ዓመት የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነፃነት ቀን፣ በዜጎች ዲፕሎማሲ፣ በቀጣይ በሚካሄዱ የቢዝነስ ፎረሞችና የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ ፕሮግራም ዙሩሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቃል አባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በቻይና ለ2ኛ ጊዜ የሚካሄደው በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቃል አቀባዩ ተናገረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲብ ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከቻይና መንግስት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟንም አንስተዋል፡፡

ከትብበሩ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ስትራቲጂና ስልት በመንደፍ በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በኢነርጂ መሰረተልማትና ግንባታ ላይ የግል ባለሃብቱን ባሳተፈ መልኩ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላት ምቹ ሁኔታ እንደፈሚጠረላት በመግለጽ÷ የሚፈጠረላትን ምቹ ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝም አቶ ነቢያት አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነፃነት ቀን በሚያዚያ 24እና25 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይከበራል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ በተካሄደው የለውጥ ሂደት በተለይም ደግሞ በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ነፃነት የተስተዋለ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዓሉን እንድታስተናግድ መደረጉንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ ከ 1 ሺህ 500 በላይ ከተለያዩ ሀገራት መንግስታትና እና አለም አቀፍ የግል ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው የተባለው።

በዜጎች ዲፕሎማሲ አማካኝነት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች መብታቸው ተከብሮ እንደኖሩና ያለ ህጋዊ ሰነድ የሚኖሩትም በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተሰራ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

በቀጣይ በሚካሄዱ የቢዝነስ ፎረሞችና የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።