ከ80 በላይ ሕገወጥ የመድሃኒት ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በመላ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሕገወጥ የመድሃኒት ንግድና ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት ከ80 በላይ የመድሃኒት ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እንዳስታወቀው ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በተደረገው የህገ ወጥ የመድሃኒት ዝውውርን የመቆጣጠርና የመከላከል ስራ ከ80 በላይ የመድሃኒት አስመጪ፣ አከፋፋይና የችርቻሮ ድርጅቶች ላይ ግኝትን መሰረት በማድረግ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ እገዳ የሚደርስ እስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ባለስልጣኑ ለዋልታ ቴሌቪዥን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ እንደገለፀው ባለፉት ሶስት ወራት የህገ ወጥ መድሃኒት ንግድና ዝውውር ለማስቆምና ጥራታቸው፣ ደህንነታቸው እንዲሁም ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪዎች ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ባደረገው ቁጥጥር የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው፣ ምንጫቸው የማይታወቅ፣ በሀገሪቱ የመድሃኒት ዝርዝር ውስጥ ያልተመዘገቡ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መድሃኒቶች እንዲሁም ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ሲፈፅሙ በተገኙ የመድሃኒት ንግድ ድርጅቶች ላይ ነው እርምጃው የተወሰደው፡፡

ህብረተሰቡ የሕገወጥ መድሃኒት ንግድና ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግም ባለስለጣኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡