የእስራኤል የደን ባለሙያዎች በሰሜን ተራሮች ፓርክ ጉዳት የደረሰባቸውን እጽዋት ለመተካት የሚያስችል ጥናት ሊያካሂዱ ነው

የእስራኤል የደን ባለሙያዎች በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጉዳት የደረሰባቸውን እጽዋት ለመተካት የሚያስችል ጥናት ሊያካሂዱ ነው ተባለ፡፡

በቀድሞዋ የእስራኤል አምባሳደር ወይዘሮ በላይነሽ ዛባድያ የተመራ የልዑካን ቡድን በቅርቡ የእሳት አደጋ የደረሰበትን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እየጎበኘ ነው፡፡

የፓርኩ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው እንደገለፁት ፓርኩን እየጎበኘ ያለው የልዑካን ቡድን አምስት የእስራኤል የደን ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።

የቡድኑ አባላት በፓርኩ የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውን ሳንቃ በር፣ እሜት ጎጎና ግጭ አካባቢዎች እየጎበኙ ነው።

ባለሙያዎቹ በፓርኩ በሚያደርጉት የሁለት ቀናት ቆይታ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውን እጸዋት መልሶ ለመተካት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ያካሂዳሉ ነው የተባለው፡፡

ለፓርኩ ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የእጸዋት ዝርያዎችን እንዴት ማልማት እንደሚቻልና ፓርኩ በአጭር ጊዜ ፈጥኖ ማገገም በሚችልበት ሁኔታ ላይ የባለሙያዎቹ ቡድን ምክረ ሃሳብ ያቀርባል ብለዋል ኃላፊው።

(ምንጭ፡-ኢዜአ)