ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የ33 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የ33 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ትብብር ልዑክ መሪ ኤሪክ ሃበርስ የተፈራረሙ ሲሆን፣ ገንዘቡ የአውሮፓ ህብረት አደጋን ለመቀነስ ለሚተገብረው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ አደጋን ለመቋቋምና ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ማህበረሰቡንና አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፥ መፈናቀልንና ህገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ ያግዛልም ነው የተባለው።

ድጋፉ ከህብረቱ አደጋን ለመቀነስ ከሚተገበረው እና ከአውሮፓ ልማት ፈንድ ፕሮጀክት የተገኘ እንደሆነም ታውቋል።

ፕሮጀክቱ በአራት አመት ተኩል በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና በደቡብ ክልል መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በፌደራልና በክልል መንግስታት የሚተገበር ይሆናል ነው የተባለው።

ቤተሰብና ማህበረሰቡን ማጠናከር፣ የክልሎችን አደጋ የመቋቋም አቅምን ማሳደግና ተጋላጭነትን መቀነስ፣ የማህበረሰቡን ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጎጅነት መቀነስ እንዲሁም የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በኢኮኖሚው መስክ ተጠቃሚ ማድረግ የፕሮጀክቱ አላማ ነው ተብሏል።

አደጋ የመቋቋም አቅምን ከማሳዳግ ባለፈም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጎልበት እና የአደጋ ጊዜ ማገገሚያ ፈንድ ማቋቋምንም ያካትታል።

(ምንጭ፡-የገንዘብ ሚኒስቴር)