ኢትዮጵያ በሆቴል ልማት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አራተኛ ደረጃን መያዟ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በሆቴል ልማት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አራተኛ ደረጃን መያዟን ጥናት አመላከተ፡፡

ደብሊው ሆስፒታሊቲ የተባለው ተቋም ባካሄደው ጥናት ግብፅ፣ ናይጀሪያ እና ሞሮኮን በመከተል ኢትዮጵያ በሆቴል ልማት በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ ሀገራት አለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ሆቴሎች በሚገኙ የመኝታ ክፍል ቁጥር ነው በሆቴል ልማት ዘርፍ ቀደሚ የሆኑት፡፡

ተቋሙ በሰሜን አፍሪካ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ እና በህንድ ውቅያኖስ ደሴት አካባቢ የሚገኙ 54 ሀገራትን በጥናቱ አካቷል፡፡

በዚህም በሰሜን አፍሪካ ደረጃውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች ግንባታ በ2018 በ2 ነጥብ 3 እድገት ሲያሳይ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት ደግሞ በ3 ነጥብ 8 ቀንሷል፡፡

በአጠቃላይ ግን ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ የ51 በመቶ እድገት በዘርፉ የተመዘገበ ሲሆን በሰሜን አፍሪካ በ58 በመቶ እና ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት ደግሞ በ47 በመቶ እድገት ተመዝግቧል፡፡

በኢትዮጵያ በ31 ሆቴሎች ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎችን ለመክፈት በፈረንጆቹ 2018 ስምምት እንደተደረሰ ያስታወሰው ጥናቱ፥ ሃገሪቱ በዘርፉ ከፍተኛ እድገት እያሳየች መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ስምምነት ከተደረሰባቸው ሆቴሎች መካከል 84 በመቶ የሚሆነውን የመኝታ ክፍል የያዙት 27 ሆቴሎች አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

ሙሉ የጥናቱ መረጃ በመጭው መስከረም ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

(ምንጭ፦ አፍሪካ ቢዝነስ ኮሙኒቲስ)