ኢትዮጵያና የአለም ባንክ የ500 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ መንግስት እና የአለም ባንክ የ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና በአለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ቱርክ ተፈራርመውታል፡፡

ድጋፉ የስነ ምህዳር አስተዳደር ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ አካባቢን ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ እንዲኖር በማድረግ በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ይዞታ ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ይህ ፕሮግራም በውጤት ተኮር ሂደት ተግባራዊ የሚደረግ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ህብረተሰቡን አሳታፊ ያደረገ የተፋሰስ ስራ ለማከናወን እና የስነ ምህዳር ጥበቃን ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል ዘገባዉ የኢዜአ ነዉ፡፡