ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አለም አቀፍ የልማት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአለም አቀፉ ልማት ማህበር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 19ኛው የአለም ባንክ አለም አቀፍ ልማት ማህበር ማሟያ ስብሰባ ላይ የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የአለም አቀፍ ልማት ማህበር ድጋፉ አስተማማኝ፣ ተገማችና አስተማማኝ የልማት ፋይናንስ ምንጭ መሆኑን አንስተዋል።

ስለሆነም የአለም አቀፍ ልማት ማህበር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በየሶስት ዓመቱ ለጋሾች በመገናኘት የአለም ባንክ አለም አቀፍ ልማት ማህበር ድጋፍን የማሟላትና የፖሊሲ ማእቀፎች ግምገማ ያካሂዳሉ።

የአለም አቀፉ ልማት ማህበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ታዳጊ ሀገራት ድህነትን ለመቀነስና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዚህ መሰረትም ከ2021 እስከ 2023 ለታዳጊ ሀገራት ለሚያደርገው ድጋፍ ከለጋሽ ሀገራት ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችለውን ስብሰባ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ድርጅቱ ከተመሰረተበት እንደ አውሮፓውያያኑ አቆጣጠር 1960 ጀምሮ 133 ሊሚሆኑ ሀገራት ለኢንቨስትመንት የሚውል ከ360 ቢሊየን ዶላር በላይ በድጋፍና እጅግ ዝቅጠኛ በሆነ ወለድ ማበደር መቻሉ ተገልጿል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የአለም ባንክ በአለም አቀፉ የልማት ትብብር ወይም አይዳ በኩል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው 75 ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

ሀገሪቱ በ2010 እና 2011 ብቻም ከአይዳ ከ5 ቢሊየን ዶላር ያላነሰ የልማት ፋይናንስ በዕርዳታ እና በብድር መልክ ድጋፍ አግኝታለች።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ በአለም ባንክ ድጋፍ ከ13 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ መሆኑ ታውቋል።