ሹር ስታርት የተሰኘው የበቆሎ ጸረ-አረም ቅድመ ብቅለት ርጭት ውጤታማ ነው ተባለ

ሹር ስታርት የተሰኘው የበቆሎ ጸረ-አረም ቅድመ ብቅለት ርጭት በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ገለጸ፡፡

በጉዳዩ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታ በምእራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ አዋራ ገማ ቀበሌ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ የአረም ሳይንስ ተመራማሪ ዶ/ር ካሳሁን ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የጸረ አረም መድሃኒቱ ከምርምር ማዕከሉ ውጭ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ሲሞከር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

አረም የሰብልን ምርት ከ30 አስከ 40 በመቶ ሊያጠፋ እንደሚችል የጠቆሙት ዶ/ር ካሳሁን፤ አረምን በማስወገድ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል በምርምር ማዕከሉ ጸረ አረም መድሃኒቱን የማላመድ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በምርምር ማዕከሉ የተገኘው  ሹር ስታርት የተሰኘው የበቆሎ ጸረ-አረም መድሃኒት በቆሎው በተዘራ እስከ ሶስተኛው ቀን ድረስ የሚረጭ ሲሆን ፤ ጸረ አረሙ ሳርና ሰፋፊ ቅጠል ያላቸውን አረሞች ያጠፋል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ በሄክታር 15 ኩንታል በቆሎ የሚመረት ሲሆን፤ ሹር ስታርን ከተጠቀሙበት ግን ከሄክታር የሚገኘውን ምርት ወደ 80 ኩንታል ያሳድገዋል ተብሏል፡፡