በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ችግኝ ተከላ በዘላቂነት ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት ሲሉ የአዲስ አበባ ጉምሩክ ኤይር ፖርት ቅንጫፍ ሰራተኞች ገለጹ፡፡
በመርሃ ግብሩ መሰረት ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላ ለተፈለገው ዓላማ እንዲበቁ በመንከባከብ ሁሉም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው በአይነታቸው ልዩ የሆኑ ችግኞችን በቦሌ አለም አቀፍ ዓየር ማረፊያ ውስጥ መትከል መጀመሩን አስታውቋል፡፡
መስሪያ ቤቱ በቅጥር ግቢው ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑ ዝርያቸው ልዩ የሆኑ ችግኞችን ለመትከል እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ዓላማውም ከሀገር አቀፍ መርሃ ግብሩ ጋር በተያያዘ የአየር ንብረቱን ለመጠበቅ ከሚደረገው በተጨማሪ አየር ማረፊያዉን ዓለም አቀፍ ስታንድርዱን ለመጠበቅ እንደሚያስችል ነው የገለፁት፡፡
ዘመቻዉን ተከትሎ የሚተከሉ ችግኞች ለተፈለገው ዓላማ እንዲደርሱ በመንከባከብ እንደሚያቆዩት የተናገሩት ሰራተኞቹ ከኤይር ፖርቱ ጋር በመሆን በርካታ ስራዎችን እደሚሰሩና ችግኞችን የመትከል ስራዉንም በጋራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ከቅጥር ግቢው ውስጥ ከሚያከናውኑት ተከላ በተጫማሪ ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑ ችግኞችን በጋራ ለመትከል እና ለመንከባከብ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸዉን የቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተገኔ ደጀን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አክለዉም ችግኞቹን እስከ መጨረሻው ድረስ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መንከባከብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡