የኢትዮ-ኬንያ ልዩ የንግድና ምጣኔ ሃብት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የሚደረገው “ስፔሻል ስታተስ” የተሰኘው ልዩ የንግድና ምጣኔ ሃብት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የኬንያ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባለሃብቶችም በዚሁ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በኢፌዴሪ ንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ጥናትና ማስተዋወቅ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ጥበቡ ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በኩል ተጠናቆ ለኬንያ መንግስት የቀረበው “ስፔሻል ስታተስ” የተሰኘው ልዩ የንግድና ምጣኔ ሃብት ስምምነት ረቂቅ ለሁለቱ ሃገራት የኢኮኖሚያ ትስስር መሰረት የሚጥል ይሆናል፡፡

ስምምነቱ በተለየ ትኩረቱም በድንበር አካባቢ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድን ህጋዊ መሰረት በማስያዝ ዜጎችን እውነተኛ የህዝብ ለህዝብ የንግድ ግንኙነት ተጠቃሚ ለማድረግ የወጠነ ነው ተብሎለታል፡፡

በርካታ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ባለሃብቶች እንዲሁም የንግድ ሰዎች የተሳተፉበት በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው የቢዝነስ ፎረም ላይ የተሳተፉ የሁለቱ ሃገራት ተወካዮችም አሁን ላይ እየተጠናከረ የመጣው የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን እንዳነሳሳቸው ነው የተናገሩት፡፡

እየተጠናከረ ባለው የሃገራቱ ዲፕሎማሲ ኢኩይቲ ባንክ እና ፋሚሊ ባንክ የተባሉ ሁለት የኬንያ ባንኮች በአዲስ አበባ ቅርንጫ ለመክፈት መሰናዳታቸው ነው የተገለጸው፡፡

በተለይም ኢኩይቲ ባንክ በተያዘው ሃምሌ ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ የሚከፍተውን ቅርንጫፉን እውን በማድረግ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ግንኙነት እንደሚያሳልጥ ታምኖበታል፡፡

በኬንያ በኩልም የቆዳ ውጤቶች፣ አበባ እና በኢትዮጵያ ለሚመረቱ በርካታ የግብርና ምርቶች መዳረሻ የሚሆን የገበያ እድል መኖሩ ተገልጿል፡፡

በአፍሪካ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ስኬት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ በዚህ በኩል ያላቸውን የዓመታት የቀጠናዊ ትብብር ስኬታቸውን ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማምጣት ብሎም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አዲስ ምዕራፍ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሁለቱ ሃገራት የ55 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ክብረ በዓልን በማስመልከት በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት ተዘጋጅቶ በነበረው የቢዝነስ ግንኙነት የውይይት መድረክ ኬንያውያን ባለሃብቶች ለንግድና ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያን ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

አዲስ አበባ እና ናይሮቢ በጆሞ ኬንያታና ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸው ይነገራል፡፡