የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከፍተኛ የታመቀ ካርበን ጋዝ ስለሚለቁ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በምርት ሂደት የሚለቁት ሙቀት አማቂ የካርበን ጋዝ ከፍተኛ በመሆኑ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት መስጠት  እንዳለባቸዉ ሚኒስትር ደኤታዉ ጠየቁ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታዉ አቶ ዮሃንስ ድንቅአየሁ ይህን ያሉት የዳንጎቴና ሙገር ፋብሪካዎች ሰራተኞች በግቢያቸዉ ችግኝ በተከሉበት ወቅት ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር ነዉ፡፡

መንግስትም በነዚህ አካባቢዎች ላይ እየደረሰ ያለዉን የአየር ንብረት ለዉጥ ተፅዕኖ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ በበኩላቸዉ በአገሪቱ ባሉት 17 ትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የአረንጓዴ ልማት መርሃግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዉ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከዚህ በፊት ላለማዉ 32 ሄክታር መሬት እዉቅና ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ችግኞቹ እንዲለሙና የተፈለገዉን አገልግሎት እንዲሰጡ ከዩንቨርስቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም ይሰራል ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላዉ ወቅት ዋልታ ያነጋገራቸዉ የመርሃግብሩ ተካፋዮች የችግኝ ተከላዉ አካባቢን ለኑሮና ስራ ምቹ በማድረግ ዉጤታማ እንድንሆን ይረዳናል ብለዋል፡፡

ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ ለእንክብካቤዉም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡